ማኅበረ ቅዱሳን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን ለማዘግየት አሁንም እየጣረ እንደሚገኝ የቤተክህነት ምንጮች አጋለጡ::
• ማኅበረ ቅዱሳን የቤተክርስቲያን ውክልና እንደሌለው ቅዱስ ሲኖዶሰ ባደረገው ልዩ ስብሰባ ከወሰነ አንድ አመት ከመንፈቅ ሆነ
• ማኅበሩ ውሳኔውን ለማስለወጥ ደጀ ሰላም የተባለ ድህረ ገጽ በመክፈት የቤተክርስቲያን አባቶችን እና አገልጋዮችን ስም በማጥፋት እና በማስፈራራት ላይ
ይገኛል
• የበሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ ማኅበሩ ከኦርቶዶክሳዊ እምነት ውጭ የሆኑ ድርጊቶችን እየፈጸመ መሆኑን መረጃዎችን በመጥቀስ አስታወቀ
ማኅበረ ቅዱሳን በሃገር ውስጥ እና ከሃገር ውጭ የቤተክርስቲያን ልጆችን ወንጌል እንዲማሩ አስተዋጽኦ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ቢገልጽም ከጊዜ ወደ ጊዜ የተነሳበትን ዓላማ እየተወ ቤተክርስቲያንን ፤አባቶችን እና ምዕመናንን በአደባባይ በማዋረድ የቤተክርስቲያንን ሃብት እና ስልጣን በእጁ ለማስገባት እየተፍጨረጨረ ይገኛል።
ይህንኑ እኩይ ተግባር ያጤኑ ብፁዓን አባቶች መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ፡ም ማኅበሩ ያለምንም ፈቃድ ቤተክርስቲያንን ወክሎ በሁሉም አህጉረ ሰብከት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም፤ አልያም በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ መዋቅር ስር በመሆን መንፈሳዊ ስራ ቢቻ እንዲሰራ፤እስካሁን የማኅበሩ አባላት በሆኑ ግለሰቦች እና በማኅበሩ ስም ያሉት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቤተክርስቲያን ሃብት እና ንብረት በትክክል እንዲያሳወቅ የተወሰነ ሲሆን በወቅቱም በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ ማኅበሩ ባለፉት አራት እና አምስት አመታት ቢቻ በቤተ ክርስቲያን ላይ የፈጸመውን ጥፋት እና ኦርቶዶክሳዊ ያልሆኑ ተግባራትን በዝርዝር ለብፁዓን አባቶች አቅርቦአል::የመንግስት ባለስልጣናትም ማኅበሩ የፖለቲካ ስራን በሃይማኖት ሽፋንማካሄዱን እንዲያቆም፤ ምንም መንፈሳዊ ይዘት የሌላቸውን የህትመት ውጤቶቻቸውን ዋቢ በማድረግ በዕለቱ አስታውቀዋል።
ነገር ግን እስካሁን ውሳኔው ተግባራዊ እንዳይሆን ማኅበሩ እንቅፋት እየሆነ ይገኛል። ይልቁንም ደጀ ሰላም የተባለ ብሎግ በመክፈት ምዕመናን በቤተክርስቲያን አባቶች እና በመምህራን ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው በማድረግ በየቦታው መከፋፈል እንዲበዛ በማድረግ ላይ ይገኛል። በተለይም በቅርቡ ከቤተ ክህነት 50 ገጽ ሰነድ አገኘሁ በማለት በውሸት ያስነበበው ዜና ከቤተክህነት እውቅና ውጭ የተደረገ ከመሆኑም በላይ በደፈናው በጥላቻ በመነሳሳት አጠቃላይ በቤተክርስቲያን ውስጥ ማንም መምህር እንደሌለና ምዕመኑ መሄዱን እንዲያቆም የሚቀሰቅስ አሉባልታ አዘል ዜና አስነብቦአል። ይህም ድርጊት የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊ ላለማድረግ ወይም ለማዘግየት ማኅበሩ የሚያደርገው ጥረት አካል ነው።ይንን ጉዳይ በተመለከተ በቅርቡ ብጹአን አባቶች ዝርዝር ሃሳብ እንደሚሰጡን ቃል ገብተዋል።
ቤተክርስቲያንን በኑፋቄ ትምህርት ለማጥቃት የተነሳሱ ግለሰቦች በየቦታው እንደሚኖሩ ይታወቃል በተለይም ለመጀመሪያ ጊዜ የተሃድሶ አመራር ሆነው የተነሱት ግለሰቦች ቀደምት የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እና አመራሮች እንደነበሩ ማንም የሚያውቀው ነው። ቅዱስ ሲኖዶስም የተወሰኑትን አውግዞ ለይቶአል። አሁንም ቤተክህነቱ ፈጽሞ ዝም ያለ ሳይሆን የቤተክርስቲያንን ጠላቶች ጠንካራ በሆነው መዋቅሮቹ ስር ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ላይ ይገኛል።
ማኅበረ ቅዱሳን ከመዋቅር ውጭ ሆኖ ቢቻውን ለመስራት እና የሚያስበው ግብ ላይ ለመድረስ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የቤተክርስቲያንን ሥርዓት የጣሰ ከመሆኑም በላይ በህግ የሚያስጠይቀው ይሆናል። ባለፈው ወር ከመጋቢ ሐዲስ በጋሻው ደሳልኝ ጋር በድሬዳዋ ተካሶ ማኅበሩ መረታቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። አሁንም የደጀ ሰላም ረፖርትሮች እንደሆኑ በታወቁት ግለሰቦች እና በማኅበረ ቅዱሳን ላይ መንፈሳዊ ኮሌጆች እና ቤተክህነት ክስ ሊመሰረቱ እንደሚችሉ የደረሰን መረጃ ይጠቁማል።
ማኅበረ ቅዱሳን ከምስረታው ጀምሮ በረካታ አመራሮች የተፈራረቁበት ሲሆን አብዛኞቹ የቀድሞ አመራሮች እና ቀደምት አባላት በተለያዩ ምክንያቶች ማኅበሩን ለቀዋል። ከምክንያቶቹም ዋናዋናዎቹ፡
• ገሚሶቹ ሃይማኖታቸውን ጥለው መናፍቅ እና ሃይማኖት የለሽ በመሆናቸው፤
• ገሚሶቹ በየጊዜው የሚለዋወጠውን የሀገሪቱን ፖለቲካ በመቀላቀል ደብዛቸው የጠፋ በመሆኑ፤
• ቀሪዎቹ ግን በማኅበሩ ውስጥ በሚነሱ የዘረኝነት፤የውስጥ ጥቅምና በስልጣን አለመግባባት የተነሳ ማኅበሩን ለቀዋል።
ማኅበሩ አሁን ካለበት ሁኔታ እንዲወጣ ስለሚደረገው ጥረት የተጠናከረ ጥናታዊ ጽሁፍ ለማቅረብ ዝግጅት ላይ እንገኛለን፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል፡፡